ምዕራፍ 40

እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው።
2 ፤ በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።
3 ፤ ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው።
4 ፤ እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።
5 ፤ አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፤ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።
6 ፤ እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ።
7 ፤ እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
8 ፤ በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?
9 ፤ እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን?
10 ፤ በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፤ በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ።
11 ፤ የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።
12 ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፤ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።
13 ፤ በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።
14 ፤ በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።
15 ፤ ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል።
16 ፤ እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።
17 ፤ ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።
18 ፤ አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፤ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።
19 ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።
20 ፤ የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል።
21 ፤ ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
22 ፤ ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።
23 ፤ እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።
24 ፤ ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?
25 ፤ በውኑ አዞውን በመቃጥን ታወጣለህን? ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?
26 ፤ ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር ጕንጩን ትበሳለህን?
27 ፤ በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን? በጣፈጠስ ቃል ይናገርሃልን?
28 ፤ በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘላለም ባሪያ ታደርገዋለህን?
29 ፤ ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ ለሴት ባሪያዎችህ ታስረዋለህን?
30 ፤ አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን? ወይስ ነጋዴዎች ያካፍሉታልን?
31 ፤ በውኑ ቁርበቱን በጭሬ፥ ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?
32 ፤ እጅህን በላዩ ጫን፤ ሰልፉን አስብ፥ እንግዲህም አትድገም።