ምዕራፍ 30

አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ።
2 ፤ ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርና የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል?
3 ፤ በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤ የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበት ወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ።
4 ፤ በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤ የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው።
5 ፤ ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል።
6 ፤ በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ።
7 ፤ በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤ ከሳማ በታች ተሰብስበዋል።
8 ፤ የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።
9 ፤ አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው።
10 ፤ ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም።
11 ፤ የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል።
12 ፤ በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ይገለብጣሉ፤ የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ።
13 ፤ ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ።
14 ፤ በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤ በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል።
15 ፤ ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤ ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች።
16 ፤ አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤ የመከራም ዘመን ያዘችኝ።
17 ፤ በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥ ጅማቶቼም አያርፉም።
18 ፤ ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤ እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ።
19 ፤ እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ።
20 ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም።
21 ፤ ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በእጅህም ብረታት አስጨነቅኸኝ።
22 ፤ በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ።
23 ፤ ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።
24 ፤ ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን?
25 ፤ ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን?
26 ፤ ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤ ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ።
27 ፤ አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤ የመከራም ዘመን መጣችብኝ።
28 ፤ ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ።
29 ፤ ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ።
30 ፤ ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤ አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች።
31 ፤ ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ።