ምዕራፍ 15

ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ንፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን? በሆዱስ የምሥራቅን ነፋስ ይሞላልን?
3 ፤ ከማይረባ ነገር፥ ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን?
4 ፤ አንተም እግዚአብሔርን መፍራት ታፈርሳለህ፤ በእግዚአብሔር ፊት አምልኮን ታስቀራለህ።
5 ፤ በደልህ አፍህን ያስተምረዋል፥ የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ።
6 ፤ የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።
7 ፤ በውኑ መጀመሪያ የተወለድህ ሰው አንተ ነህን? ወይስ ከተራሮች በፊት ተፀነስህን?
8 ፤ የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን? ወይስ ጥበብን ለብቻህ አድርገሃልን?
9 ፤ እኛ የማናውቀውን አንተ የምታወቀው ምንድር ነው? ከእኛ ዘንድስ የሌለው የምታስተውለው ምንድር ነው?
10 ፤ በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ።
11 ፤ በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥ በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን?
12 ፤ ልብህስ ለምን ይወስድሃል? ዓይኖችህስ ለምን ይገለምጣሉ?
13 ፤ በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን እስከ ማንሣት ደርሰህ፤ ይህንም ቃል ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ።
14 ፤ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?
15 ፤ እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።
16 ፤ ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥ ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?
17
18 ፤ ምድሪቱ ለብቻቸው ተሰጥታ የነበረች፥
19 ፤ በመካከላቸውም እንግዳ ያልገባባቸው ጠቢባን። ከአባቶቻቸው ተቀብለው የተናገሩትን ያልሸሸጉትንም፥ እገልጥልሃለሁ፥ ስማኝ፤ ያየሁትንም እነግርሃለሁ።
20 ፤ ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፥ ከግፈኛ በተመደቡለት በዓመታት ሁሉ በሕመም ይጣጣራል።
21 ፤ የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፤ በደኅንነቱም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል።
22 ፤ ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ አያምንም፥ ሰይፍም ይሸምቅበታል።
23 ፤ ተቅበዝብዞም። ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፤ የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል።
24 ፤ መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፤ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል፤
25 ፤ እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ ላይ ደፍሮአልና፥
26 ፤ በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው ጕብጕብ እየሠገገ ይመጣበታልና፥
27 ፤ በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥ ስቡንም በወገቡ ላይ አድርጓልና፥
28 ፤ በተፈቱም ከተሞች ውስጥ፥ ሰውም በሌለባቸው፥ ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና
29 ፤ ባለጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፤ ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፤
30 ፤ ከጨለማ አይወጣም፤ ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥ አበባዎቹም ይረግፋሉ።
31 ፤ ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን።
32 ፤ ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥ ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33 ፤ እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፤ እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል።
34 ፤ የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፥ የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች።
35 ፤ ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥ ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።