ምዕራፍ 7

በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን?
2 ፤ አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥
3 ፤ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ።
4 ፤ በተኛሁ ጊዜ። መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ።
5 ፤ ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፤ ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል።
6 ፤ ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥ ያለ ተስፋም ያልቃል።
7 ፤ ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፤ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።
8 ፤ የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፤ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም።
9 ፤ ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም።
10 ፤ ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።
11 ፤ ስለዚህም አፌን አልከለክልም፤ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፤ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ።
12 ፤ ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን?
13 ፤ እኔም። አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥
14 ፤ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤
15 ፤ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች።
16 ፤ ሕይወቴን ናቅኋት፤ ለዘላለም ልኖር አልወድድም። የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ።
17 ፤ ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥
18 ፤ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ?
19 ፤ የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው?
20 ፤ ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ? ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ? ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ?
21 ፤ ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።