ምዕራፍ 33

ነገር ግን፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ።
2 ፤ እነሆ፥ አፌን ከፍቻለሁ፥ አንደበቴም በትናጋዬ ተናግሮአል።
3 ፤ ቃሌ የልቤን ቅንነት ያወጣል፤ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ።
4 ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ።
5 ፤ ይቻልህ እንደ ሆነ መልስልኝ፤ ቃልህንም አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም።
6 ፤ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ።
7 ፤ እነሆ፥ ግርማዬ አታስፈራህም እጄም አትከብድብህም።
8 ፤ በጆሮዬ ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፥ እንዲህም ብለሃል።
9 ፤ እኔ ያለ መተላለፍ ንጹሕ ነኝ፤ ያለ ነውር ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፤
10 ፤ እነሆ፥ ምክንያት አግኝቶብኛል፥ እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤
11 ፤ እግሬን በግንድ አጣበቀ፥ መንገዴንም ሁሉ ተመለከተ።
12 ፤ እነሆ፥ አንተ በዚህ ጻድቅ አይደለህም፤ እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል ብዬ እመልስልሃለሁ።
13 ፤ አንተ። ለቃሌ ሁሉ አይመልስልኝም ብለህ፥ ስለ ምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ?
14 ፤ እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።
15 ፤ በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥
16 ፤ በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥
17 ፤ ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤
18 ፤ ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።
19 ፤ ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል።
20 ፤ ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች።
21 ፤ ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፤ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል።
22 ፤ ነፍሱ ወደ ጕድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች።
23 ፤ የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጕም መልአክ ቢገኝለት፥
24 ፤ እየራራለት። ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥
25 ፤ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል።
26 ፤ ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ሞገስን ይሰጠዋል ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፤ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል።
27 ፤ እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ። እኔ በድያለሁ፥ ቅኑንም አጣምሜአለሁ፤ የሚገባኝንም ብድራት አልተቀበልሁም፤
28 ፤ ነፍሴ ወደ ጕድጓድ እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል።
29 ፤ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፤
30 ፤ ይህም ነፍሱን ከጕድጓድ ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው።
31 ፤ ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።
32 ፤ ነገር ቢኖርህ መልስልኝ፤ ትጸድቅ ዘንድ እወድዳለሁና ተናገር።
33 ፤ ያለዚያም እኔን ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።