ምዕራፍ 3

ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ።
2 ፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህ አለ።
3 ፤ ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥ ያም። ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት።
4 ፤ ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤ እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥ ብርሃንም አይብራበት።
5 ፤ ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፤ ዳመናም ይረፍበት፤ የቀን ጨለማ ሁሉ ያስፈራው።
6 ፤ ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፤ በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤ በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።
7 ፤ እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፤ እልልታ አይግባበት።
8 ፤ ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት።
9 ፤ አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤ ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥ የንጋትንም ቅንድብ አይይ፤
10 ፤ የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥ መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።
11 ፤ በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም? ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም?
12 ፤ ጕልበቶች ስለ ምን ተቀበሉኝ? ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ?
13 ፤ አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤ አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤
14 ፤ የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥
15 ፤ ወይም ቤታቸውን ብር ከሞሉ ወርቅም ካላቸው መኳንንት ጋር፥
16 ፤ ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፥ ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።
17 ፤ ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፤ በዚያም ደካሞች ያርፋሉ።
18 ፤ በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።
19 ፤ ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፤ ባሪያም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።
20 ፤ በመከራ ላሉት ብርሃን፥ ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥
21 ፤ የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥
22 ፤ መቃብርን ባገኙ ጊዜ በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?
23 ፤ መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥ እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ?
24 ፤ ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥ ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።
25 ፤ የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።
26 ፤ ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፤ ነገር ግን መከራ መጣብኝ።