ምዕራፍ 32

ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ።
2 ፤ ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው።
3 ፤ ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ።
4 ፤ ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር።
5 ፤ ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ።
6 ፤ የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ። እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ።
7 ፤ እንደዚህም አልሁ። ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር።
8 ፤ ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል።
9 ፤ በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።
10 ፤ ስለዚህም። ስሙኝ፤ እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ።
11 ፤ እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤ ብልሃታችሁን አዳመጥሁ።
12 ፤ እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም።
13 ፤ እናንተም። ጥበብን አግኝተናል፤ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ።
14 ፤ እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፤ እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም።
15 ፤ እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፤ የሚናገሩትንም አጡ።
16 ፤ እነርሱ አልተናገሩምና፥ ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን?
17 ፤ እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥ እውቀቴንም እገልጣለሁ፤
18 ፤ እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥ በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና።
19 ፤ በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥ ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ።
20 ፤ ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፤ ከንፈሬን ገልጬ እመልሳለሁ።
21 ፤ ለሰው ፊት ግን አላደላም፤ ሰውንም አላቈላምጥም።
22 ፤ በማቈላመጥ እናገር ዘንድ አላውቅምና፤ ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር።