ምዕራፍ 17

መንፈሴ ደከመ፥ ዘመኔ አለቀ፥ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል።
2 ፤ አላጋጮች በእኔ ዘንድ አሉ፥ ዓይኔም በማስቈጣታቸው አደረች።
3 ፤ አሁንም አንተ መያዣ ሆነህ ተዋሰኝ፤ ከእኔ ጋር አጋና የሚመታ ማን ነው?
4 ፤ ልባቸውም እንዳያስተውል ከልክለኸዋል፤ ስለዚህ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም።
5 ፤ ለብዝበዛ ባልንጀሮቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዓይን ይጨልማል።
6 ፤ ለሕዝብም ምሳሌ አደረገኝ፤ በፊቱ ላይ ጺቅ እንደሚሉበት ሰው ሆንሁ።
7 ፤ ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ፈዘዘች፥ ብልቶቼም ሁሉ እንደ ጥላ ሆኑ።
8 ፤ ቅኖች ሰዎች በዚህ ነገር ይደነቃሉ፥ ንጹሕም በዝንጉው ላይ ይበሳጫል።
9 ፤ ጻድቅ ግን መንገዱን ያጠነክራል፥ እጁም ንጹሕ የሆነ ሰው ኃይልን እየጨመረ ይሄዳል።
10 ፤ ነገር ግን እናንተ ሁሉ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፤ በእናንተም ዘንድ ብልሃተኛ አላገኝም።
11 ፤ ዕድሜዬ አለፈች፤ አሳቤና የልቤ መሣርያ ተቈረጠ።
12 ፤ ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤ ብርሃኑም ወደ ጨለማ የቀረበ ይመስላቸዋል።
13 ፤ ተስፋ ባደርግ ሲኦል ቤቴ ናት፤ ምንጣፌንም በጨለማ ዘርግቻለሁ።
14 ፤ መበስበስን። አንተ አባቴ ነህ፤ ትልንም። አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ።
15 ፤ እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው?
16 ፤ አብረን በመሬት ውስጥ ስናርፍ፥ ወደ ሲኦል ይወርዳል።