ምዕራፍ 106

ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።
2 የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል?
3 ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።
4 አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤
5 የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ።
6 ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም።
7 አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።
8 ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው።
9 የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው።
10 ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው።
11 ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም።
12 በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።
13 ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።
14 በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።
15 የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።
16 ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው።
17 ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤
18 በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።
19 በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።
20 ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።
21 -
22 ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ።
23 እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።
24 የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥
25 በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
26 -
27 በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው።
28 በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ።
29 በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ።
30 ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤
31 ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።
32 -
33 በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ።
34 እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤
35 ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ።
36 ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው።
37 ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤
38 የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች።
39 በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ።
40 የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ።
41 ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው።
42 ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ።
43 ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ።
44 እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤
45 ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።
46 በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው።
47 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።
48 ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።