ምዕራፍ 61

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር።

አምላክ ሆይ፥ ልመናዬን ስማ፥ ጸሎቴንም አድምጥ።
2 ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ።
3 ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ሆነኸኛልና መራኸኝ።
4 በድንኳንህ ለዘላለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ፤
5 አቤቱ፥ አንተ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ ስምህንም ለሚፈሩ ርስትህን ሰጠሃቸው።
6 ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀን ትጨምራለህ፥ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናሉ።
7 በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይኖራል፤ ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትንና እውነትን አዘጋጅለት።
8 እንዲሁ ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ።