ምዕራፍ 54

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል። እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ።
2 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤
3 እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም።
4 እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው።
5 ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው።
6 ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤
7 ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።