ምዕራፍ 93

በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር።

እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት።
2 ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ።
3 አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ።
4 ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው።
5 ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።