ምዕራፍ 57

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ጉዳት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ።
2 ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።
3 ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ።
4 ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው።
5 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።
6 ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ።
7 ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ።
8 ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።
9 አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤
10 ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ።
11 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።