ምዕራፍ 138

የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።
2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና።
3 በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፤ ነፍሴን በኃይልህ በብዙ አጸናሃት።
4 አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና።
5 በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ፤ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና።
6 እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል።
7 በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች።
8 እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ ለዘላለም ነው፤ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል።