ምዕራፍ 3

ከልጁ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸ ጊዜ የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው።
2 ብዙ ሰዎች ነፍሴን። አምላክሽ አያድንሽም አልዋት።
3 አንተ ግን አቤቱ፥ መጠጊያዬ ነህ፥ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ።
4 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር እጮሃለሁ ከተቀደሰ ተራራውም ይሰማኛል።
5 እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ።
6 ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም።
7 ተነሥ፥ አቤቱ፤ አምላኬ ሆይ፥ አድነኝ፤ አንተ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና፥ የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና።
8 ማዳን የእግዚአብሔር ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።