ምዕራፍ 68

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
2 ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኅጥኣን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
3 ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው።
4 ለእግዚአብሔር ተቀኙ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ፤ በፊቱም ይደነግጣሉ።
5 እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።
6 እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።
7 አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥
8 ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ።
9 አቤቱ፥ የሞገስን ዝናብ ለርስትህ አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው።
10 እንስሶችህ በውስጡ አደሩ፤ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ።
11 እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ የሚያወሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው።
12 የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች።
13 በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ።
14 ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ።
15 የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፤ የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው።
16 የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው፤ በእውነት እግዚአብሔር ለዘላለም ያድርበታል።
17 የእግዚአብሔር ሰረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው።
18 ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ።
19 እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል።
20 አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።
21 ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፥ በኃጢአት የሚሄድንም የጠጕሩን አናት ይቀጠቅጣል።
22 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ከባሳን አመጣቸዋለሁ፥ ከባሕርም ጥልቅ እመልሳቸዋለሁ፥
23 እግሮችህ በደም ይረገጡ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶች ላይ ይሆን ዘንድ።
24 የአምላኬ የንጉሥ መንገድ በመቅደሱ፥ አቤቱ፥ መንገድህ ተገለጠ።
25 አለቆች ቀደሙ፥ መዘምራንም ተከተሉ፤ ከበሮን በሚመቱ በቈነጃጅት መካከል።
26 እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ አመስግኑት።
27 ወጣቱ ብንያም በጕልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች።
28 አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው።
29 በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ።
30 በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው።
31 መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
32 የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ።
33 በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል።
34 ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው።
35 እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።