ምዕራፍ 26

የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ እኔ በየውሃቴ ሄጃለሁና ፍረድልኝ፤ በእግዚአብሔርም አምኛለሁና አልናወጥም።
2 አቤቱ፥ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን።
3 ምሕረትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ።
4 በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም።
5 የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም።
6 እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥
7 የምስጋናን ድምፅ እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ።
8 አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።
9 ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ።
10 በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች።
11 እኔ ግን በየውሃቴ ሄጃለሁ፤ አድነኝ ማረኝም።
12 እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።