መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 113
 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርንም ስም አመስግኑ።
2  ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።
3  ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን።
4  እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው።
5  እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤
6  በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤
7 -
8  ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤
9  መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ሃሌ ሉያ።