ምዕራፍ 147

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር።

እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው።
2 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል።
3 ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል።
4 የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።
5 ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም።
6 እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል።
7 ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፤
8 ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም።
9 ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል።
10 የፈረስን ኃይል አይወድድም፥ በሰውም ጭን አይደሰትም።
11 እግዚአብሔር በሚፈሩት፥ በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል።
12 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ፥
13 ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና።
14 በወሰንሽም ሰላምን አደረገ፥ የስንዴንም ስብ አጠገበሽ።
15 ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፥ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል።
16 አመዳዩን እንደ ባዘቶ ይሰጣል፤ ጉሙን እንደ አመድ ይበትነዋል፤
17 በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፤ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል?
18 ቃሉን ልኮ ያቀልጠዋል፤ ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችንም ያፈስሳል።
19 ቃሉን ለያዕቆብ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል።
20 ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፥ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም። ሃሌ ሉያ።