ምዕራፍ 95

የዳዊት ምስጋና መዝሙር።

ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል።
2 በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤
3 እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና።
4 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው።
5 ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት።
6 ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤
7 እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና።
8 በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ።
9 የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ ሥራዬንም አዩ።
10 ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ።
11 ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።