ምዕራፍ 64

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ ወደ አንተ በለመንሁ ጊዜ ጸሎቴን ስማኝ፥ ከጠላትም ፍርሃት ነፍሴን አድን።
2 ከክፉዎች ሸንጎ ከዓመፀኞችም ብዛት ሰውረኝ።
3 እንደ ሰይፍ ምላሳቸውን አሰሉ፤ መራራ ነገርን ለማድረግ፥
4 ንጹሕንም በስውር ለመንደፍ ቀስትን ገተሩ፤ ድንገት ይነድፉታል አይፈሩምም።
5 ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፤ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፤ ማንስ ያየናል? ይላሉ።
6 ዓመፃን ፈልጓት፥ ሲፈትኑም አለቁ፤ የሰው የውስጥ አሳቡና ልቡ የጠለቀ ነው፥
7 እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። የድንገትም ፍላጻ፤ ያቈስላቸዋል፤
8 አንደበታቸው ያሰናክላቸዋል፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ይደነግጣሉ።
9 ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ።
10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።