ምዕራፍ 89

የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት።

አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘላለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ።
2 እንዲህ ብለሃልና። ምሕረት ለዘላለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል።
3 ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ።
4 ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ።
5 አቤቱ፥ ሰማያት ተኣምራትህን እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ።
6 እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል?
7 በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው።
8 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል።
9 የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።
10 አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው።
11 ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትህ።
12 ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል።
13 ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።
14 የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።
15 እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ።
16 በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤
17 የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።
18 ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና።
19 በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ እንዲህም አልህ። ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ።
20 ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።
21 እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች።
22 ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።
23 ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።
24 እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።
25 እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።
26 እርሱ። አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል።
27 እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።
28 ለዘላለምም ምሕረቴን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው።
29 ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ።
30 ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፤
31 ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፤
32 ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ።
33 ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፤
34 ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም።
35 ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።
36 ዘሩ ለዘላለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል።
37 ለዘላለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፤ ምስክርነቱ በሰማይ የታመን ነው።
38 አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ የቀባኸውንም ጣልኸው።
39 የባሪያህንም ኪዳን አፈረስህ፥ መቅደሱንም በምድር አረከስህ።
40 ቅጥሩን ሁሉ ጣልህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ።
41 መንገድ አላፊም ሁሉ ተናጠቀው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ።
42 የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ።
43 የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም።
44 ከንጽሕናውም ሻርኸው፥ ዙፋኑንም በምድር ጣልህ።
45 የዙፋኑንም ዘመን አሳነስህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው።
46 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ፊትህን ትመልሳለህ? እስከ መቼስ ቍጣህ እንደ እሳት ይነድዳል?
47 ችሎታዬ ምን እንደ ሆነ አስብ፤ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን?
48 ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው?
49 ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ምሕረትህ ወዴት ነው?
50 አቤቱ፥ የባሪያዎችህን ስድብ፥ በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥
51 አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን የቀባኸውን ዘመን የሰደቡትን አስብ።
52 እግዚአብሔር ለዘላለም ይባረክ። ይሁን ይሁን።