ምዕራፍ 33

የዳዊት መዝሙር።

ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል።
2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት።
3 አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤
4 የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና።
5 ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።
6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤
7 የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው።
8 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ።
9 እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።
10 እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል።
11 የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው።
12 እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።
13 እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ።
14 ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥
15 እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል።
16 ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም።
17 ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም።
18 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥
19 ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ።
20 ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና።
21 ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና።
22 አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።