ምዕራፍ 65

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ጸሎት ይቀርባል።
2 ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል።
3 የዓመፃ ነገር በረታብን፤ ኃጢአታችንንስ አንተ ይቅር ትላለህ።
4 አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው ምስጉን ነው፤ ከቤትህ በረከት እንጠግባለን።
5 ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን።
6 በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል።
7 የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ።
8 ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ፥ በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ፤ የጥዋትንና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ።
9 ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና።
10 ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ።
11 በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።
12 የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።
13 ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።