ምዕራፍ 67

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር።

እግዚአብሔር ይማረን ይባርከንም፥ ፊቱንም በላያችን ያብራ፤
2 በአሕዛብ ሁሉ መካከል ማዳንህን፥ መንገድህንም በምድር እናውቅ ዘንድ።
3 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ።
4 ለአሕዛብ በቅን ትፈርድላቸዋለህና፥ አሕዛብንም በምድር ላይ ትመራለህና አሕዛብ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ።
5 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ።
6 ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።
7 እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል።